አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ ፕሮጀክት ስራ እየተፋጠነ ነው፡፡
በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ በቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ በባህርዳር ከተማ ውስጥ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክትን በመስክ የስራ ቅኘት ተጎብኘቷል። ባህርዳር ከተማ ውስጥ ከሚገኘው ከነባሩ አባይ ወንዝ ድልድይ 2 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡ የግንባታ ስራው ከተጀመረ ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን የግንባታ አፈጻጸሙ በእቅዱ መሰረት በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ። የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ከዲዛይን ስራዎች እና የካምፕ ግንባታዎች መጠናቀቅ በተጨማሪ በዋነኝነት ከመሬት በታች የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ቁፋሮ እና አርማታ ሙሌት ስራ ነው እየተከናወነ የሚገኘው፡፡ ከመሬት በታች የሚቀበሩት እነዚህ የክብ ቅርፅ ያላቸው የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች በዲዛይኑ መሰረት ከዝቅተኛው 14 ሜትር እስከ ከፍተኛው 23 ሜትር ድረስ ወደታች የሚቀበሩ ናቸው፡፡ የአንዱ የቋሚ ተሸካሚ መሰረት የመሀል መለኪያ ስፋት በድልድዩ የዳር እና ዳር ተሸካማዎች 1.5 ሜትር ሲሆን የመካከል ተሸካሚዎች ደግሞ 1.8 ሜትር ነው፡፡ 380 ሜትር የሚረዝመው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ ስራ ፕሮጀክት በእስካሁኑ አፈፃፀም በአጠቃላይ ድልድዩን ለመሸከም ከሚያስፈልጉ 88 የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ውስጥ 48 የሚሆኑት የቁፋሮ እና የአርማታ ሙሌት ስራ ማከናወን ተችሏል፡፡ ቀሪዎቹን የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶችም በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ ግንባታ ለማከናወን የሚወጣውን 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት ነው የሚሸፈነው፡፡ 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው የአባይ ወንዝ ድልድይ በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ ነው እየተገነባ የሚገኘው ። ከዚህም በተጨማሪም ግንባታው የብስክሌት ተጠቃሚዎች መስመር እንዲሁም 5 ሜትር የእግረኛ መሄጃንም አካቷል፡፡ የድልድዩን ግንባታ በተቆጣጣሪነት እና በአማካሪነት እያገለገሉ የሚገኙት የቱርኩ ቦቴክ እና የአገር ውስጥ አማካሪው እስታዲያ በጋራ በመሆን ነው። በአይነቱ እና በዲዛይን ጥበቡ በሀገራችን ቀዳሚ የሆነው የአባይ ወንዝ ድልድይ የግንባታ አይነት በተሻሻለ መንገድ በገመድ የተወጠረ (Extradosed cable steyed Bridge) የድልድይ ዲዛይን ነው፡፡ ድልድዩን በአዲስ መልክ ለመገንባት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ነባሩ የአባይ ወንዝ ድልድይ ከተገነባ 60 አመታትን በማስቆጠሩና በአገልግሎት ብዛት ለተደጋጋሚ ጉዳት በመዳረጉ ነው ፤ በተጨማሪም የድልድዩ የጎን ስፋት 10 ሜትር ከመሆኑ አንጻር በመስመሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ በመፍጠሩ ነው ፡፡ ድልድዩ አለም አቀፋዊ ደረጃውን በጠበቀ ሁናቴ ዘመናዊ በሆነ መልኩ መገንባቱ የሀገር ቋሚ የቱሪስት መስህብ በመሆን እረገድ ፍይዳው የጎላ ነው ። አፍሪካን በመንገድ መሰረተ ልማት ማገናኘት ያለመው ትራንስ አፍሪካ ሃይ ወይ የተሰኘው ከግብፅ ካይሮ ተነስቶ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ድረስ የሚዘልቀው ዋና መንገድ አካል በመሆኑ በዚህ አፍሪካ አቀፍ ባህርይ ባለው መንገድ ላይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅምን ለኢትዮጵያ በማስገኘት ዘመኑን የሚመጥን ድልድይ መገንባት ጠቀሜታው ከሀገር አልፎ አህጉራዊ ፋይዳው የጎላ ነው። የድልድዩ ግንባታ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
Go Back