Loading..

ስለ አባይ ወንዝ ድልድይ

የአባይ ወንዝ ታሪክ እና አባይ ወንዝን የሚያርጡ ድልድዮች

አባይ(Abay) ማለት ታላቅ ከወንዞች ሁሉ አብይ ማለት ነው ። አባይ የናይል ወንዝ ታላቁ ገባር ሲሆን መነሻውም ኢትዮጵያ ነው። ታላቁ ወንዝ 70 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱን ወንዞች የውሃ መጠን ይይዛል፡፡ የአባይ ወንዝ 1450 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ ርዝመት አለው፡፡ ከዚህ አጠቃላይ ርዝመት ውስጥ 800 ኪ.ሜ ያህሉን በሀገር ውስጥ ይጓዛል ፡፡ ከደቡባዊ የጣና ሀይቅ በመነሳት የሀገሪቱን ሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ እየተጠማዘዘ ወደ ሱዳን የሚገባው አባይ 400 ኪሜ ያህሉን በሸለቆ ውስጥ ስለሚያልፍ ወንዙን ለመሻገር እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ከቀሪው ግማሽ የሀገሪቱ ክፍል ጋር ያለድልድይ መገናኘት አዳጋች ነው፡፡

ምንም እንኳን ወደ ጣና ሀይቅ የሚገቡ ገባር ወንዞች ቢኖሩም ግሽ አባይ ተብላ የምትታወቅ አንዲት አነስተኛ ምንጭ የአባይ መነሻ እንደሆነች ይታመናል፡፡ የአባይ ወንዝ “ጥቁር አባይ” ወይም “ብሉ ናይል” እየተባለ ቆይቶ የኢትዮጲያን ግዛት ተሻግሮ ወደ ሱዳን በመግባት ካርቱም ከተማ ላይ ነጭ አባይ ከሚባለው አጋሩ ጋር እንደተቀላቀለ ናይል በሚል መጠሪያ ወደ ሜዲቴራንያን ባህር ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ የድልድይ ግንባታ አጀማመር መነሻን መለስ ብለን ስንቃኝ በ16ኛው መ.ክ.ዘ ከአባይ ፏፏቴ አልፈን እንደተጓዝን በምናገኘው ጠባብ ገደል ላይ አባይ ወንዝን የሚያቋርጥ የመጀመሪያው የድንጋይ ድልድይ ተገነባ፡፡ ይህ በ16 12 ዓ.ም በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት በአባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የመጀመርያው ድልድይ የእንቁላል ድልድይ ይባላል፡ ፡ ድልድዩ ልክ እንደዛሬው ቴክኖሎጂ በቅጡ ባልዳበረበት ዘመን በኢትዮጵያ የድልድይ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶት በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቦ የምናገኘው እንቁላልን እንደ ሲሚንቶ ግብአትነት በመጠቀም የተሰራ አሁንም ድረስ የእንቁላል ድልድይ ተብሎ የሚጠራው ድልድይ ነው፡፡ የ400 ዓመት እድሜ ባለጸጋው የእንቁላል ድልድይ ባለ 8 አፍ ወይም በእንግሊዘኛው አጠራር arch bridge የሚባለው ነው፡፡ በኢትዮጵያ እስከ አሁን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዞችን የሚያሻግሩ ድልድዮች መገንባታቸው ይታወቃል፡፡

ከነዚህም ውስጥ ታላቁን አባይ ወንዝ የሚሻገሩ ድልድዮች ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡ እንግዲህ አባይ በትውልድ ሀገሩ በኢትዮጵያ 800 ኪ.ሜ ያህል ሲጓዝ ከ17ኛው ክፍለዘመን እስከ ቅርብ ድረስ አባይን ለመሻገር 10 ያህል ድልድዮች በተለያዩ ቦታዎች እንደተገነቡለት ታሪክ ይናገራል ፡፡

የድልድይ ግንባታ ስራ በኢትዮጵያ አባይ ወንዝ ላይ ሀ ብሎ ጀመረ እነሆ ዛሬ 400 አመታትን ጠብቆ በልዩ ታሪካዊ አጋጣሚ እዛው አባይ ወንዝ ላይ እጅግ ዘመናዊ ድልድይ ግንባታ ስራ ለማከናወን የሚያስችል ትልቅ ታሪካዊ አሻራ ማኖር ተቻለ ፡፡ የአባይ ድልድይ ለኢትዮጵያውያን ኩራት ከዛም አልፎ ለአገራችን አዲስ የታሪክ አሻራ በማኖር ወደ ብልጽግና ጉዞ የሚያሻግረን ድልድያችን ተምሳሌት ነው፡፡



ስለ አባይ ድልድይ

አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ 380 ሜትር ይረዝማል፡፡ ድልድዩ 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን በግራና በቀኝ በአንድ ግዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፡፡ ከዛም ባለፈ ለብስክሌት ተጠቃሚዎች መንገድና 5 ሜትር የእግረኛ መሄጃን ያካተተ ነው፡፡ የድልድዩን ስራ በብር 1,437,000,000.00 የሚያካሂደው ዓለም አቀፉ የቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ተቋራጭ ነው፡፡ የስራ ተቋራጩ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ጋር የውል ስምምነቱ ያካሄደው መጋቢት 18 ቀን 2011 ዓ.ም ነው፡፡

ግንባታውን የቁጥጥርና የማማከር ሥራ የሚያካሂዱት ቦቴክ ቦስፈረስ የተባለ የቱርክ አማካሪ ድርጅት ከስታዲያ ኢንጅነሪንግ ስራዎች ድርጅት ከተባለ አገር በቀል ንኡስ አማካሪ ድርጀት ጋር በጋራ በመሆን ነው፡፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት የግንባታ ወጪው የሚሸፈነው ድልድዩ በሶስት አመት ግዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡