Loading..

ዜና

የዓባይ ድልድይ በምህንድስናው ዘርፍ የእውቀት ሽግግር የተደረገበት ዘመናዊ ግንባታ መሆኑን ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 29/2014 ዓ.ም (አሚኮ) በተለያዩ የምህንድስና ሙያ ተሰማርተው የሚሰሩና የሚመሩ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለሙያዎች አዲሱን የዓባይ ወንዝ ድልድይ ጎብኝተዋል፡፡ በምህንድስናው ዘርፍ ያለውን የእውቀት ሽግግር ማጠናከር ደግሞ የጉብኝቱ ዓላማ ነው ተብሏል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ የሚገነባው ዘመናዊ የዓባይ ድልድይ ከውበቱ እና የትራንስፖርት ዘርፍ ጥቅሙ ባሻገር በምህንድስናው ዘርፍ ሀገራዊ የእውቀት ሽግግር የተካሄደበት ነው ያሉት በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የምህንድስና ባለሙያ የሆኑት ኢንጂነር አብርሃም አብደላ ናቸው፡፡ ድልድዩ በውጭ ባለሙያዎች የሚገነባ ቢሆንም በርካታ የሀገር ውስጥ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነው ያሉት ኢንጅነር አብርሃም በዘርፉ በቂ ልምድ እና እውቀት ተገኝቶበታል ብለዋል፡፡ የዓባይ ድልድይ በአይነቱ እና በዘመናዊነቱ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከሚያስተዳድራቸው ድልድዮች የተለየ ነው ያለን ደግሞ ከጎብኝዎቹ መካከል አንዱ የሆነው አዲስህይዎት ታደሰ ነው፡፡ ድልድዩ የከተማዋን ውበት እና የአካባቢውን የትራንስፖርት ፍሰት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለረጂም ጊዜ እንዲያገለግል ታስቦ እየተገነባ ነው ያለው ኢንጂነር አዲስሕይዎት ሀገሪቱ በምህንድስናው ዘርፍ መሻሻሎችን እያሳየች ለመሆኗ አንድ ማሳያ ነው ብሏል፡፡ ከዋናው መሥሪያ ቤት በሥራ አፈጻጸም እና በሪፖርት ግብረ መልስ ሲከታተሉት የነበሩትን ግንባታ በአካል ማየታቸው እንዳስደሰታቸው የተናገሩት ደግሞ ኢንጂነር ከድጃ ሙሃመድ እና ኢንጂነር ቤዛ ታየ ናቸው፡፡ ድልድዩ በዓይነቱ የተለየ፣ ዘመናዊ እና አዳዲስ የምህንድስናውን ዘርፍ ቴክኖሎጂ የተጠቀመ ነው ያሉት ባለሙያዎቹ ለኢትዮጵያዊያን የምህንድስና ባለሙያዎችም የእውቀት ሽግግር የተገኘበት ነው ብለዋል፡፡




Go Back