Loading..

ዜና

አዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ እየተተገበረ ነው

በባህር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝላይ እየተገነባ ያለው አዲሱ የዓባይ ድልድይ በአይነቱ ልዩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዘርፉ ለተሰማሩ የፕሮጀክት አመራሮችና ሰራተኞች የእውቀት ሽግግር እያስገኘ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለፀ። በባህር ዳር ከተማ ዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው አዲሱ የዓባይ ድልድይ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክት አመራሮች እና ሠራተኞች ተጎብኝቷል። በአስተዳደሩ የመንገድ ሀብት ሲስተም ማኔጅመንት ዳይሬክተር ኢንጅነር አብርሃም አብደላ እንዳሉት፣ አዲሱ የዓባይ ድልድይ ግንባታ ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ፕሮጀክት ትግበራ ድረስ ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጅ ተጠቅሞ እየተተገበረ የሚገኝ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከ5 ሺህ በላይ ድልድዮችንና ከ40 ሺህ በላይ ካልበርቶችን የሚያስተዳድር ቢሆንም የዓባይ ድልድይ ፕሮጀክት የተለየ መሆኑን አመልክተዋል። ይህ ፕሮጀክት በሌሎች ፕሮጀክቶች ለተመደቡ አመራሮችና ሰራተኞች አዳዲስ እውቀት፣ ልምድና ተሞክሮ የሚያስገኝ መሆኑንም ተናግረዋል። በሀገራችን በድልድይ ግንባታ እና አስተዳደር ዘርፍ የእውቀት ሽግግር በማምጣት በቀጣይ ሌሎች የዓለም ሀገሮች የደረሱበት የእድገት ደረጃ ለመድረስ በር የሚከፍት መሆኑንም አስረድተዋል። ፕሮጀክቱ የባህር ዳር ከተማን ገፅታ በመገንባት የቱሪስት መስህብ በመሆን የሚያገለግል መሆኑን በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የፕሮጀክቱ ቡድን መሪ ኢንጅነር አዲስህይወት ታደሰ ገልጸዋል። ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመት እና 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው በመሆኑ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድን አካቶ እየተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል። ከድልድዩ በተጨማሪ 51 ሜትር ስፋት ያለው የ5 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድ ግንባታን፣ የድልድይ ላይ መብራቶችና የትራፊክ ምልክቶችን ያካተተ ዘመናዊ ፕሮጀክት እንደሆነ ተናግረዋል። የድልድዩ መገንባት ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች የትራፊክ ፍሰትን በማሳለጥ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት መፋጠን ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በአስተዳደሩ የምስራቅ ሪጅን ፕሮጀክት ኢንጅነር ከድጃ ሙሃመድ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በመጎብኘታቸውም አዲስ እውቀት፣ ልምድ፣ ክህሎትና የቴክኖሎጅ ሽግግር ለማግኘት አስችሏቸዋል። አክለውም ያገኙትን እውቀት በመጠቀም በቀጣይ በሚሰሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በመስሪያ ቤቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚመሩና የሚሰሩ መሃንዲሶች አዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታን ከጎበኙ በኋላ በምልከታቸው ላይ ያተኮረ ውይይት ማካሄዳቸውን ኢዘኤ ዘግቧል።።




Go Back