Loading..

ዜና

እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ አሳሰቡ፡፡

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 11/2012 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ፡፡ በዘንድሮው በጀት ዓመት በባሕር ዳር ከተማ በፌዴራል እና በክልል የበጀት ምንጭ እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶችን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህን ጨምሮ የክልሉ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተመልክተዋል፡፡ በከተማዋ ሕዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የዓባይ ወንዝ ተለዋጭ ድልድይ ፕሮጀክትን ጨምሮ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተሠሩ ያሉ የአስፓልት መንገዶች፣ የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ግንባታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ከተጎበኙት መካከል ናቸው፡፡ እየተገነቡ ያሉት ፕሮጀክቶቹ ከ456 ሚሊዮን ብር በላይ በከተማ አስተዳደሩ እና በክልሉ በጀት የተመደበላቸው መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተጋረድ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ የግብዓት በተለይ (የሬዳሽ) አቅርቦት ችግር ገጥሞት እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ በባሕር ዳር እየተሠሩ ላሉ መሠረተ ልማቶች አብዛኞቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ተባባሪ እንደነበሩ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሐሪ ታደሰ (ዶክተር) ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ “አንዳንድ በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በሥራችን ላይ ጫና አሳርፈዋል” ብለዋል፡፡ ለከተማዋ ዕድገትም እንቅፋት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ “በሚሠሩ ፕሮጀክቶች ላይ ጥብቅ ክትትል በማድረግና በሕገ ወጦች ላይ ርምጃ በመውሰድ የከተማችንን ዕድገት እናፋጥናለን” ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ በምልከታቸው እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ግንባታው የተጀመረውና በፌዴራል መንግሥት በተመደበ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ወጭ በሦስት ዓመታት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚገነባው የዓባይ ወንዝ ተለዋጭ ድልድይ ግንባታ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነም ርእሰ መሥተዳድሩ ተናግረዋል፡፡ የድልድዩ ግንባታ ስምንት በመቶ ላይ መድረሱንም ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ዘጋቢ፡- ይርጋለም አስማማው Link: https://amharaweb.com/%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%88%A0%E1%88%A9-%E1%8B%AB%E1%88%89-%E1%88%98%E1%88%A0%E1%88%A8%E1%89%B0-%E1%88%8D%E1%88%9B%E1%89%B6%E1%89%BD-%E1%8A%A5%E1%8A%95%E1%8B%B2%E1%8C%A0%E1%8A%93%E1%89%80/




Go Back